Assosa University

አሶሳ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ ተሳትፎ የተራቆተ መሬትን ለዘላቂ ልማት መልሶ በማልማት ላይ ይገኛል

አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ማህበረሰብን መሠረት ያደረገ መሬትን መልሶ ማልማት የሚችል ለ4 ዓመታት የሚቆይ ፕሮጀክት ቀርጾ በአብርሃሞ ወረዳ ሩባላጌዳ ቀበሌ የተራቆተ መሬት ተቀብሎ በማልማት ሥነ-ምህዳሩን ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ እየሰራ ይገኛል።

የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡመር ሸሪፍ ኘሮጀክቱን በጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት ፕሮጀክቱ ሥነ-ምህዳራዊ መልሶ ማቋቋም ብቻ ሳይሆን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን ማሻሻል ላይም ያተኮረ መሆኑን አስረድተዋል። የተራቆተ መሬትን በማልማት ተነሳሽነቱ ዘላቂ የግብርና ልማትን ለማረጋገጥ፣ ብዝሃ ህይወትን ለማሳደግ እና የረጅም ጊዜ የኑሮ መሻሻል እድሎችን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት የፕሮጀክቱን ስራ የበለጠ ለማጠናከርና የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች ከቀበሌው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት በመጪው ክረምት የሚተከሉ ችግኞችን ከወዲሁ በማዘጋጀት ስራውን በቁርጠኝነት እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።

በተጨማሪም ስራውን በአግባቡ ለማከናወን የሚያግዙ እንዲሁም የቀበሌው ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ከአባይ ተፋሰስ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ግምታቸው 200,000 ብር የሚያወጡ የግብርና ቁሳቁሶች በድጋፍ መሰጠታቸውን ገልጸዋል።

የማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክተር ዶ/ር ተፈራ ተሾመ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በዑራ ወረዳ በአምባ ሶስት ቀበሌ ስራዉ ተጀምሮ ጥሩ ውጤት በማሳየቱ በአብርሃሞ ወረዳም ፕሮጀክቱ እንዲተገበር መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው ማህበረሰብ የተተከሉ እና በቀጣይ ለሚተከሉ ችግኞችን ከከብቶች ንክኪ ነጻ እንዲሆኑ ተገቢው ጥበቃ በማድረግ በተደረገው የቁሳቁስ ድጋፉም የቀበሌ ማህበረሰብ በመሬት መልሶ ማልማት ሥራዎች ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ዶ/ር ተፈራ አሳስበዋል።

የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶክተር አልማዝ ደቼ እንዳሉት ፕሮጀክቱ ማህበረሰቡን ማጠናከር፣ አካባቢን መጠበቅ እና ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ዘላቂነት አስተዋፅዖ ማድረግ የመሳሰሉ ሁለገብ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ተናግረዋል።

ከአባይ ተፋሰስ አሶሳ ቅርንጫፍ የተገኘው ድጋፍ የፕሮጀክቱን ውጤታማነት በማጎልበት የህብረተሰቡን ቁርጠኝነት እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

የቀበሌው ማህበረሰብ አባላትም እየተሠራ ያለው ስራ የአካባቢያያቸውን በመለወጥ ለዘላቂ የወደፊት ተስፋ መስጠት እንደጀመረ በመግለጽ ዩኒቨርሲቲዉ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች በቀጣይ በይበልጥ እንዲጠናከር አሳስበዋል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ የማህበራዊ ገፆቻችን ይከተሉ

‎For Additional Information

‎Twitter:Assosa University (@AssosaU) / X

‎Website: www.asu.edu.et

‎WhatsApp group: https://whatsapp.com/channel/0029Vau844l9xVJkZ3GXR21P

‎Facebook: https://www.facebook.com/AssosaUniversityOfficial

‎Telegram: https://t.me/+J9ZDxvCigO0yN2Nk

‎Email: pir@asu.edu.et

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *