




ዩኒቨርሲቲዉ በዛሬዉ ዕለት የቀድሞ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችና ም/ፕሬዚዳንቶች ፣የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነጥብ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ ነፊሳ አልመሃዲ፣የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልልሉ ም/ል ፕሬዚዳንትና የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ጌታሁን አብዲሳ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች፣ የሴኔት አባላት እንዲሁም የተመራቂ ተማሪ ቤተሰቦች በተገኙበት የምረቃ ሥነሥርዓቱ ተካሂዷል።
በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ አጭር የዩኒቨርሲቲዉን የሥራ እንቅስቃሴና የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ያሬድ ሙሉ በዲጂታላይዜሽንና አስተዳደር ዘርፍ፣በአካዳሚክጥራት ማረጋገጥ፣በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም በግንባታ ፕሮጀክት የተከናወኑና በመከናወን ላይ ያሉ ሥራዎችን በአጭሩ ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልእክት ዛሬ የለበሳችሁት የምረቃ ጋወንና የምትቀዳጁት ኮፍያ ዝም ብሎ የተገኘ የክብር ጌጥ ሳይሆን ከጀርባዉ የብዙ ሌሊት እንቅልፍ ማጣት፣ የቤተ መጽሐፍት ድካምና የፈተና ጭንቀት እልህ አስጨራሽ ጥረት ዉጤት የሆነ የድል አክሊል ነዉና እንኳን ደስ አላችሁ እንኳን የሥራ ዉጤታችሁን ለማየት አበቃችሁ ብለዋል።
በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ ሀገራችን ኢትዮጵያ የእናንተን እዉቀት ፣ጉልበት እና አዲስ አስተሳሰብ ትፈልጋለችና በሄዳችሁበት ቦታ ሁሉ የሰላም፣ የአንድነትና የልማት አምባሳደር እንድትሆኑ ሲሉ ለተመራቂዎቹ አደራ ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዉ በዛሬዉ ዕለት በቅድመ ምረቃ 202 እና በድህረ ምረቃ 471 በድምሩ 673 ተመራቂዎች በደማቅ ሥነሥርዓት ያስመረቀ ሲሆን በትምህርት ክፍልና በተቋም ደረጃ ከፍተኛ ዉጤት ያስመዘገቡ ተመራቂዎች ከክብር እንግዶች፣ከቀድሞ እና ከአሁኑ የዩኒቨርሲቲዉ አመራሮች የሜዳልያና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ከአጠቃላይ ተመራቂዎች ከወንዶች ኪዳነ ማሪያም ዉለታዉ ከፋርማሲ ትምህርት ክፍል 3.98 GPA እና ከሴት ተመራቂዎች ኢማን ዲልሰባ በተመሳሳይ ከፋርማሲ ትምህርት ክፍል 3.77 GPA በማምጣት የሜዳልያና የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል።
ለተጨማሪ መረጃ የማህበራዊ ገፆቻችን ይከተሉ
For Additional Information
Twitter:Assosa University (@AssosaU) / X
Website: www.asu.edu.et
WhatsApp group: https://whatsapp.com/channel/0029Vau844l9xVJkZ3GXR21P
Facebook: https://www.facebook.com/AssosaUniversityOfficial
Telegram: https://t.me/+J9ZDxvCigO0yN2Nk
Email: pir@asu.edu.et