Assosa University

በዩኒቨርስቲው የቀድሞ አመራሮች የእዉቅናና ምስጋና ፕሮግራም ተዘጋጀ፤ የቀድሞ አመራሮች ፎረም ምስረታ ተበሰረ

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ሰባት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ለመሩት ዶ/ር ከማል አብዱራሂም እና የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ል ፕሬዚዳንት ለነበሩት ዶ/ር አብዱልሙህስን ሀሰን የአሁኑ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የእዉቅና እና ምስጋና ፕሮግራም በዛሬዉ ዕለት ተዘጋጅቷል።

‎ፕሮግራሙ በተመሳሳይ አዲስ ለተመደቡት የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ያሬድ ሙሉ የእንኳን ደህና መጡ አቀባበል ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነዉ።

‎አዲሱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ያሬድ ሙሉ በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ የዩኒቨርሲቲዉን ከምሥረታ ጀምሮ እስከ አሁን በመማር ማስተማሩ፣ በምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግሩ እንዲሁም በማህበረሰብ ጉድኝት የተሰሩ ሥራዎችን ዘርዝረዉ ከዚህ በፊት ዩኒቨርሲቲዉን ላገለገሉ አመራሮች የላቀ ክብር እና ምስጋና አቅርበዋል።

‎ከዚህም በተጨማሪ የቀደምት አመራሮች ከጎኔ በመሆን ለዩኒቨርሲቲዉ እድገት በጋራ እንዲንሰራ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

‎የቀድሞዉ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ከማል አብዱራሂም በተደረገላቸዉ የእዉቅና እና ምስጋና ተግባር መደሰታቸዉን ገልጸዉ መሪነት የአንድ ሰዉ ሥራ ብቻ አለመሆኑንና ተቋማት በግለሰቦች ብቻ የሚቆሙ ባለመሆናቸዉ የአሠራር ሥርዓቶች፣ አደረጃጀቶች እና እሴቶች ስራዎችን እንድሰሩ ማድረግ እንደሚጠበቅ በመድረኩ አስገንዝበዋል።

‎ዶ/ር ከማል በተጨማሪም ከዚህ በኋላም ከተቋሙ ጎን ሆኜ ህዝቤን እና ሀገሬን አገለግላለሁ ሲሉ ቃል ገብተዉ ወንድሜ ዶ/ር ያሬድ በእኔ የተተኩት አዲሱ ፕሬዚዳንት በሚፈልጉት ሁሉ ከጎናቸዉ በመሆን የሚጠበቅብኝ ሁሉ ለማገዝ እሰራለሁ ብለዋል።

‎በተመሳሳይም ዶ/ር አብደልሙህስን ሀሰን ከምወደዉ ተቋም ሠራተኛ እና አመራር ይህን መሠል በክብር አሸኛኘት ስለተደረገልኝ ከልብ አመሠግናለሁ ካሉ በኋላ በዩኒቨርሲቲዉ ቆይታየ እጅግ ያማረ ነበር ሲሉ ገልጸዋል።

‎ዶ/ር አብዱልሙህስን አክለዉም ዶ/ር ያሬድ ሙሉ ከዚህ በፊት በአለም አቀፍ ትብብር ልምድ ያካበቱ በመሆናቸዉ የዩኒቨርሲቲዉን አለም አቀፋዊነት አጋር አጠናክረዉ እንደሚሰሩበት ያላቸዉን እምነት ገልጸዉ በጋራ እና በትብብር መስራት እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።

‎አቶ አብዱልከሪም አብዱራሂም የአሶሳ ከተማ ከንቲባ እና ዩኒቨርሲቲዉ ሥራ አመራር ቦርድ አባል በበኩላቸዉ ባስተላለፉት መልዕክት የቀድሞ አመራሮች ዩኒቨርሲቲዉ በብዙ ፈተናዎች ወቅት በነበረበት ጊዜ ወደ አመራርነት የመጡ ሲሆኑ ተቋሙ አሁን ላለበት ደረጃ ያደረሱ በመሆናቸዉ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል ብለዋል።

‎አቶ አብዱልከሪም እንደ ከተማ ከንቲባነታቸዉ እና እንደስራ አመራር ቦርድ አመራርነታቸዉ ዩኒቨርሲቲዉን እና የዩኒቨርሲቲዉን ማህበረሰብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚሰሩ እና ዶ/ር ያሬድ ሙሉ አሶሳ ላይ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆኜ እሰራለሁ ብለህ በመምጣጥህ እናከብርሃለን ብለዋል።

በመጨረሻም የዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ያሬድ ሙሉ ለዩኒቨርሲቲው ዕድገት የቀድሞው አመራሮች ፎረም ማቋቋም አስፈላጊ እንደሆነ ገልፀዉ ለዚህም በዛሬዉ መድረክ ላይ ፎረሙ በይፋ መቋቋሙን አብስረዋል። በቅርብ ጊዜ ዉስጥ በሚመቻቸዉ ፕሮግራም ዩኒቨርሲቲዉን ከምስረታ ጀምሮ በፕሬዚዳንትነትና ምክትል ፕሬዘዳንትነት የመራችሁ የቀድሞ አመራሮች ጋር ተገናኝተን ስለዩኒቨርስቲው እንመክራለን፤ ለዚህ በጎ ዓላማ ከጎናችን እንደትሆኑ ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ለተጨማሪ መረጃ የማህበራዊ ገፆቻችን ይከተሉ

Twitter:Assosa University (@AssosaU) / X

Website: www.asu.edu.et

WhatsApp group: https://whatsapp.com/channel/0029Vau844l9xVJkZ3GXR21P

Facebook: https://www.facebook.com/AssosaUniversityOfficial

Telegram: https://t.me/+J9ZDxvCigO0yN2Nk

Email: pir@asu.edu.e

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *