

አሶሳ ዩኒቨርሲቲ በአሶሳ ከተማና በአካባቢው እየተስተዋለ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስና የእግረኞችን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ የሚያስችል የመንገድ ደህንነት ፕሮጀክት እያከናወነ መሆኑን አስታዉቋል።
የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክተር ዶ/ር ተፈራ ተሾመ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶችን ቀርፆ እየሰራ መሆኑን ገልፀዉ፣ በአሶሳ ከተማና አካባቢው የትራፊክ ደህንነትን ለማጠናከር ለትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የተለያዩ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን እና የማህበረሰብ ንቅናቄ ሥራዎች ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰባዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እየተገበረው ባለው በዚህ ፕሮጀክት፣ በተለይም ከአሶሳ-ሆሞሻ እና ከአሶሳ-ባምባሲ መስመር የትራፊክ ምልክቶች ተከላ፣ የፍጥነት መቀነሻ ግንባታዎች እንዲሁም የአቅጣጫ መቀየሪያ የመትከል ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ዶ/ር ተፈራ ገልፀዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ የትራፊክ ፍሰትን በመቆጣጠር ከትራፊክ አደጋ የፀዳ የመንገድ ደህንነት እንዲፈጠር ማድረግ ሲሆን፣ በተለይም በአደጋ ተጋላጭ ቦታዎች የትራፊክ ምልክቶችን መትከል፣ የትራፊክ መጨናነቅን መቀነስ፣ የእግረኛ ማቋረጫዎችን በመገንባት የእግረኞችን ደህንነት ማስጠበቅ እና ለማህበረሰቡ የመንገድ ደህንነት ግንዛቤ መፍጠር እንደሆነ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ መምህር ተገኝ ሞታ ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ መሰራት የትራፊክ አደጋዎችን በእጅጉ እንደሚቀንስና እግረኞች ያለምንም ስጋት የእግረኛ ማቋረጫዎችን በመጠቀም መንገድ እንዲሻገሩ እንደሚያስችልም ተጠቁሟል።
በተጨማሪም አሽከርካሪዎች የትራፊክ ምልክቶችን በትክክል እንዲረዱና እንዲከተሉ በማስቻል በድንገት የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በአካባቢው የትራፊክ ደህንነትን በማሻሻል የሰው ሕይወትና ንብረት ከአደጋ ለመጠበቅ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል፡፡
