


በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ከሰኔ 4 እስከ 12/2018 ዓ.ም ለተመራቂ ተማሪዎች እና በድጋሚ ለሚፈተኑ ተማሪዎች የሚሰጠውን የመውጫ ፈተና (Exit Exam) በተሳካ ሁኔታ ለማስፈጸም ለፈተና አስፈጻሚዎችና ሱፐርቫይዘሮች ኦሬንቴሽን እና የመመሪያ ገለጻ ተሰጥቷል።
ገለጻውን የሰጡት የዩኒቨርሲቲው የፈተና ማዕከል ኃላፊ አቶ ጌትነት ታመነ ሲሆኑ፣ በፈተና ሂደት ወቅት ለተፈታኞች የተፈቀዱና የተከለከሉ ተግባራት፣ የፈተና ደንቦችን እና ደንብ ጥሰቶች የሚያስከትሏቸውን ውጤቶች በዝርዝር አብራርተዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ያሬድ ሙሉ ለፈተና አስፈጻሚዎችና ሱፐርቫይዘሮች እንኳን ወደ ዩኒቨርሲቲው በደህና መጣችሁ በማለት አቀባበል ያደረጉ ሲሆን፣ በቆይታቸው ወቅት እንደ ቤታቸው እንዲሰማቸው ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ዶ/ር ያሬድ በተጨማሪም በሀገራችን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ የመውጫ ፈተናው በሕግ፣ በደንብና በሙያዊ ሥነ-ምግባር መሠረት እንዲካሄድ ሁሉም አካላት የሚገባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።
ከዩኒቨርሲቲው የፈተና ማዕከል በተገኘ መረጃ መሠረት፣ ከ3,200 በላይ ተፈታኞች በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የፈተና ማዕከል በመገኘት ፈተናቸውን በበይነ መረብ የሚወስዱ መሆኑ ታውቋል።
በሌላ በኩል፣ በዩኒቨርሲቲው ለአቅም ማሻሻያ (Remedial Program) ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው ፈተና በሰላምና በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ተገልጿል።
