



አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በአሶሳ ከተማ፣ በሆሞሻና ፓዌ ወረዳዎች እንዲሁም በግልገል በለስ ከተማ በሚገኙ 13 የጤና ተቋማትን ወደ ሞዴል የጤና ተቋማት ለማሸጋገር እየተተገበረ ያለውን የጤና መረጃ ሥርዓት (Health Information System-HIS) ማሻሻያ ፕሮጀክት አፈጻጸም ገምግሟል።
በመድረኩ የተገኙት የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ያሬድ ሙሉ እንደገለጹት፣ መረጃ በጤናው ዘርፉ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልፀው ዩኒቨርሲቲው የክልሉን የጤና ተቋማት በማጠናከርና በማደራጀት የጤና መረጃ ሥርዓቱን ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዑመር ሽሪፍ በበኩላቸው፣ በጤና ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል የመረጃ አብዮት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዩኒቨርሲቲው ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር ፕሮጀክቱን በተሳካ ሁኔታ እያስፈጸመ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ አፈጻጸም ግምገማ የጤና መረጃ ማዕከላት መደራጀት፣ የDHIS2 ሪፖርት ስርዓት አጠቃቀም መሻሻል፣ የመረጃ ጥራት መጠናከር እና የባለሙያዎች አቅም መጎልበት የተመዘገቡ ዋና ዋና ስኬቶች መሆናቸው ተገልጿል።
እንዲሁም በምክርና ክትትል፣ በአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እና በቴክኒካዊ ድጋፍ የታገዙ የጤና ተቋማት በጤና መረጃ አያያዝ ዘርፍ አበረታች ውጤቶችን እንዳስመዘገቡ ተገምግሟል።
በተለይም ተቋማቱ በDHIS2 ሪፖርት አቀራረብ፣ በመረጃ ጥራት ማረጋገጫ ሥራዎች እና በአፈጻጸም ክትትል ረገድ ጉልህ መሻሻል እንዳሳዩ ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል የመሠረተ ልማትና የቴክኖሎጂ ግብዓት ፣ የHIS መደበኛ መሣሪያዎች እጥረቶች እና መረጃን ለውሳኔ አሰጣጥ የመጠቀም ባህል ውስንነት እንደ ዋና ተግዳሮቶች ተለይተው ቀርበዋል። እነዚህ ጉዳዮችም በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶባቸው ሊሠራ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
መድረኩ በክልሉ ሞዴል የጤና ተቋማትን ለመፍጠር እና በመረጃ ላይ የተመሰረተ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ቀጣይነት ያለው ትብብርና ጠንካራ የመረጃ አጠቃቀም ባህል ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነ ተገልጿል።
በመድረኩ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ አመራሮች፣ የአሶሳ ዞን እና የአሶሳ ከተማ ጤና መምሪያ ኃላፊዎች፣ የአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል አመራሮች፣ የወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች፣ የጤና ጣቢያ ኃላፊዎች፣ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ከጎንደር ዩኒቨርሲቲና ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ምሁራንና መምህራን ተሳትፈዋል።