Assosa University

ዩኒቨርሲቲ በመጪው ክረምት 63 ሺህ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ

አሶሳ ዪኒቨርሲቲ በ2018 ዓ.ም የክረምት ወቅት 63 ሺህ ችግኞችን በዩኒቨርሲቲው ግቢ እና በአካባቢው ወረዳዎች እንዲሁም ለህብረተሰቡ ለማሰራጨት የሚያስችል ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።

በዩኒቨርሲቲው የደን አያያዝና እንክብካቤ መምህር እና የችግኝ ጣቢያው አስተባባሪ መ/ር አህመድ አሊ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው በ2017 ዓ.ም ከ73 ሺህ በላይ ችግኞችን በማፍላት በዩኒቨርሲቲው ግቢ እና ከግቢው ውጭ በአብርሃሞ እና ዑራ ወረዳዎች የችግኝ ተከላ ማከናወኑን አስታውሰዋል።

በእነዚህ መርሃ ግብሮች የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና የአካባቢው ነዋሪዎች በንቃት በመሳተፍ በጎርፍ የተጎዱና የተራቆቱ መሬቶችን በማልማት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ገልፀዋል።

መምህር አህመድ አሊ አክለውም ለመጪው የክረምት ወቅት ዩኒቨርሲቲው ለአሶሳ አካባቢ ተስማሚና ምርታማ የሆኑ የቡና ዝርያዎችን ከጅማ የምርምር ማዕከል በማምጣትና በማባዛት በአጠቃላይ 18 ዓይነት ዝርያዎችን የያዙ 63 ሺህ ችግኞችን ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

እነዚህ ችግኞች ከሰኔ 15/2018 ዓ.ም. ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ግቢ፣ በጎርፍ በተራቆቱ በአካባቢው ወረዳዎች ላይ እንደሚተከሉ እንዲሁም ለህብረተሰቡ እንዲሰራጩ ዝግጅቱ መጠናቀቁ ተገልጿል።

በሌላ በኩል የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አብዲሳ አበበ እንደገለጹት፣ በዩኒቨርሲቲው የምርምር ማዕከል ውስጥ የቀርቀሃ፣ የማንጎ፣ የሙዝ፣ የአቮካዶ፣ የቡና እና የፓፓያ እርሻዎች ተለይተው በስራ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እንደ ዶ/ር አብዲሳ ገለጻ፣ እነዚህ የምርምርና ስልጠና ማዕከላት ለመምህራን የምርምር ስራዎችን ለማከናወን፣ ለተማሪዎች ተግባራዊ ትምህርትን ለማጠናከር እና ለአካባቢው ማህበረሰብ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎች አካባቢውን ከጎርፍ አደጋ ለመከላከል፣ የአፈር መሸርሸርን ለመቀነስ እና የአረንጓዴ አሻራ ሽፋንን ለማስፋፋት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ይህ ስራ ላለፉት አራት ዓመታት በተከታታይ ሲከናወን የቆየ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት በኡራ እና በአብርሃሞ ወረዳዎች በጎርፍ የተራቆቱ መሬቶችን ለማከም የችግኝ ተከላ በማከናወን የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ዶ/ር አብዲሳ ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም ከመንግስት ተቋማት፣ ከማህበረሰቡ እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር የአካባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎችን የበለጠ አጠናክሮ እንደሚያከናውን ተገልጿል።

ስለ ዩኒቨርሲቲዉ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የማህበራዊ ገፆቻችን ይከተሉ

Twitter:Assosa University (@AssosaU) / X

Website: www.asu.edu.et

WhatsApp group: https://whatsapp.com/channel/0029Vau844l9xVJkZ3GXR21P

Facebook: https://www.facebook.com/AssosaUniversityOfficial

Telegram: https://t.me/+J9ZDxvCigO0yN2Nk

Email: pir@asu.edu.et

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *