



አዲሱ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ያሬድ ሙሉ የአሶሳ ፕሬዚዳንት ከነበሩት ከዶ/ር ከማል አብዱራሂም በዛሬዉ ዕለት የስራ ርክክብ የማድረግ ተግባር በመጀመር ከዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት ጋር ትውውቅ አድርገዋል፡፡
የርክክብ መርሃ ግብሩን ዶ/ር ከማል አብዱራሂም ለአዲሱ ፕሬዚዳንት እና ከትምህርት ሚኒስቴር ለመጡ የስራ ሀላፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ያስጀመሩ ሲሆን ከዩኒቨርሲቲው ምስረታ እና እሳቸዉ ወደ አመራርነት ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ሰባት ዓመታት በመማርና ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች በርካታ ተግዳሮቶችን በማለፍ ዉጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።
በቀጣይም አዲሱ አመራር ከዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር የተጀመሩ ስኬቶችን በማስቀጠል እና ሌሎች ከሚመለከተዉ አካል ጋር በመነጋገር መሟላት የሚገባቸዉን ጉዳዮች በማሳካት ተቋሙ ከላቀ ደለጃ ደርሶ ማየት እንደሚመኙ ገልጸዋል፡፡
ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኙት ደ/ር አሳልፍ ወ/ጊወርጊስ እና አቶ ጫኔ አደፍርስ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ብዝሃነትን የሚጠብቅ እና ኢትዮጵያን የሚመስል የአመራር ምደባ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዉ አዲሱ ፕሬዚዳንት ያላቸውን የቀድሞ የአመራር ልምድ በመጠቀም የተጀመሩ ሥራዎችን በቁርጠኝነት እንዲያስቀጥሉ አሳሰበዋል።
አዲሱ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ያሬድ ሙሉ በበኩላቸዉ ለተደረገላቸው ልዩ አቀባበልና የስራ ርክክብ ስነ-ስርዓት ምስጋና አቅርበው፣ በዶ/ር ከማል አብዱራሂም በሳል አመራርና ቁርጠኝነት የተከናወኑ ሥራዎች አድንቀዉ እነዚህን ስኬቶች ለማስቀጠልና ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። በተጨማሪም ዶ/ር ያሬድ ዩኒቨርሲቲው የህብረተሰቡ ጸጋ በመሆኑ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ከክልሉ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
የስራ ርክክቡ ስነ-ስርዓት የተጀመረዉ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የሴኔት እና የካዉንስል አባላት እንዲሁም ከትምህርት ሚኒስቴር የመጡ አመራሮች ባሉበት ሲሆን ደ/ር ከማል አብዱራሂምም ዩኒቨርሲቲዉ እናያከናወናቸዉ ያሉ እና ለወደፊት ሊያከናዉናቸዉ ያቀዳቸዉን ሪፖርት አቅርበዋል። በቀጣይ ቀናትም ያላለቁ የርክክብ እና የትዉዉቅ ስራዎች የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ የማህበራዊ ገፆቻችን ይከተሉ
Twitter:Assosa University (@AssosaU) / X
Website: www.asu.edu.et
WhatsApp group: https://whatsapp.com/channel/0029Vau844l9xVJkZ3GXR21P
Facebook: https://www.facebook.com/AssosaUniversityOfficial
Telegram: https://t.me/+J9ZDxvCigO0yN2Nk
Email: pir@asu.edu.et