


የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ያሬድ ሙሉ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በትምህርት ላይ ከሚገኙ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ጋር በበይነ መረብ (Online) የውይይት መድረክ አካሂደዋል።
ውይይቱ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በትምህርት ላይ የሚገኙ መምህራንን ለመተዋወቅ፣ የትምህርታቸውን ሂደትና የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለማወቅ እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው ልማትና አካዳሚያዊ ተግባራት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የታለመ እንደሆነ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ያሬድ ሙሉ ገልጸዋል።
በውይይቱ መምህራኑ ያሉበትን የትምህርት ሁኔታ በመግለጽ በአካዳሚክ እንቅስቃሴዎች፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ተቋማት ጋር የሚደረግ ግንኙነትና ትብብር (Partnership)፣ የውስጥ ገቢ ማመንጫ ሥራዎችን ማስፋፋት እና ሌሎች የልማት ተግባራት ላይ ለመሳተፍ ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።
በመጨረሻም ዶ/ር ያሬድ ለዩኒቨርሲቲው እድገትና ስኬት ሁሉም የተቋሙ ማህበረሰብ እና ባለድርሻ አካላት የራሳቸውን አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ በማቅረብ በውይይቱ የተነሱ ሃሳቦች በዩኒቨርሲቲው የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅዶች ውስጥ ተካትተው በተግባር እንደሚፈጸሙ ገልጸዋል።