Assosa University

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞና የአሁን አመራሮች የአመራሮች ፎረም ምስረታና የወደፊት የሥራ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት አካሄዱ

የቀድሞና የአሁኑ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች የዩኒቨርሲቲውን የአመራሮች ፎረም ምስረታ እና የወደፊት የሥራ አቅጣጫዎች በተመለከተ ሰፊ ውይይት አካሂደዋል።

ውይይቱ ተቋማዊ ቀጣይነትን ለማጠናከር፣ የአመራር ልምዶችን ለማጋራት እና የዩኒቨርሲቲውን የልማት አቅጣጫ በጋራ ለማጎልበት ያለመ እንደሆነ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ያሬድ ሙሉ ተናግረዋል።

በውይይቱ መክፈቻ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ያሬድ ሙሉ የፎረሙን ዓላማ፣ አስፈላጊነት፣ የአደረጃጀት መርሆዎች፣ የአባልነት መስፈርቶች፣ የሥራ መስኮች እና የወደፊት የትብብር አቅጣጫዎችን የሚያብራራ የውይይት መነሻ ሰነድ አቅርበዋል።

ዶ/ር ያሬድ እንዳብራሩት፣ ፎረሙ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ያገለገሉ አመራሮችን በአንድ ማዕቀፍ በማሰባሰብ የተቋሙን ተቋማዊ ትውስታ ለማጠናከር፣ የልምድና የዕውቀት ልውውጥን ለማጎልበት፣ የምርምርና የልማት ተነሳሽነቶችን ለማበረታታት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ስትራቴጂያዊ አቅጣጫዎች ላይ የአማካሪነት ሚና እንዲወጣ የታሰበ መሆኑን ገልጸዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ፎረሙ የተቋማዊ ቀጣይነትን ለማረጋገጥ እና የልምድና የዕውቀት ሽግግርን ለማጠናከር ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መድረክ መሆኑን ገልጸው፣ የፎረሙ አወቃቀር ግልጽ፣ ተሳታፊና ዘላቂ እንዲሆን የሚያግዙ ገንቢ ሀሳቦችን አቅርበዋል።

የአሁኑ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችም ከቀድሞ አመራሮች የሚሰበሰበው ልምድና ዕውቀት ለአካዳሚክ ልህቀት፣ ለተቋማዊ አቅም ግንባታ እና ለዩኒቨርሲቲው ተልዕኮ ስኬታማ አፈጻጸም ከፍተኛ እሴት እንዳለው በመግለጽ፣ ፎረሙ በመደበኛነት እየተጠናከረ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ሀሳቦችን አቅርበዋል።

በውይይቱ ማጠቃለያ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የቀድሞ ዩኒቨርሲቲ አስ/ል/ም/ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ጌታሁን አብዲሳ፣ ተሳታፊዎች ያቀረቧቸው ገንቢ አስተያየቶችና ምክረ ሀሳቦች በፎረሙ መነሻ ሰነድ ውስጥ ተካተው ምስረታው በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ እንዲተገበር አሳስበዋል። በተጨማሪም የቀድሞና የአሁኑ አመራሮች በአንድነት በመሥራት ዩኒቨርሲቲውን በትምህርት፣ በምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት እና በተቋማዊ ልህቀት የላቀ ደረጃ ለማድረስ የጋራ ኃላፊነት መውሰድ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

በመጨረሻም ተሳታፊዎቹ የአመራሮች ፎረሙ ለተሻለ አስተዳደር፣ ለተቋማዊ ቀጣይነት፣ ለልምድና ዕውቀት ሽግግር፣ ለጋራ ራዕይ ግንባታ እና ለዘላቂ ተቋማዊ እድገት ጠንካራ መሠረት እንደሚፈጥር በመግለጽ ውይይታቸውን በስምምነት አጠናቀዋል።

ለተጨማሪ መረጃ የማህበራዊ ገፆቻችን ይከተሉ

‎For Additional Information

‎Twitter:Assosa University (@AssosaU) / X

‎Website: www.asu.edu.et

‎WhatsApp group: https://whatsapp.com/channel/0029Vau844l9xVJkZ3GXR21P

‎Facebook: https://www.facebook.com/AssosaUniversityOfficial

‎Telegram: https://t.me/+J9ZDxvCigO0yN2Nk

‎Email: pir@asu.edu.et

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *