



(አሶሳ ዩኒቨርሲቲ፣ ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም) አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሦስቱም ዞኖች ለተመረጡ ከ180 በላይ ከ9ኛ እስከ 11ኛ ክፍል ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው የSTEM (Science, Technology, Engineering and Mathematics) ማዕከል በመቀበል የ45 ቀናት የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጠ ይገኛል።
በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የምርምር፣ ማህበረሰብ ጉድኝትና ኢንዱስትሪ ትስስር አስተባባሪ ዶ/ር ሀብታሙ ጌትነት እንደገለጹት፣ ፕሮግራሙ ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸው በንድፈ ሐሳብ ያገኙትን እውቀት በዩኒቨርሲቲው ቤተ ሙከራዎች (Laboratories) በተግባር እንዲያጠናክሩ እድል የሚፈጥር ሲሆን፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላቸውን ክህሎትና የፈጠራ አቅም በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።
በተጨማሪም ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲውን አካዳሚያዊና ማህበራዊ አካባቢ እንዲለማመዱ፣ ከተለያዩ ዞኖች የመጡ እኩዮቻቸው ጋር ልምድና ዕውቀት እንዲለዋወጡ እንዲሁም ለወደፊቱ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎች እንዲሆኑ ጠንካራ መሠረት እንደሚጥልም አስረድተዋል።
በSTEM ማዕከሉ ትምህርታቸውን ከሚከታተሉት ተማሪዎች መካከል ከፋሮ ትምህርት ቤት የመጣው ተማሪ ሄኖክ ጸጋዬ እና ከቡለን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጣችው ተማሪ ብዙነሽ ዓለም በሰጡት አስተያየት፣ ዩኒቨርሲቲው ይህን የመማር ዕድል በማመቻቸቱ ያላቸውን ምስጋና ገልጸው፣ ትምህርቱን ከንድፈ ሐሳብ ባለፈ በቤተ ሙከራ በተግባር በመከታተላቸው የላቀ ግንዛቤና አዳዲስ ልምዶችን እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ አክለውም ዩኒቨርሲቲው በክልሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርትን በማጠናከር፣ የወጣቶችን የፈጠራ ብቃት በማሳደግ እና ለሀገር ልማት የሚያስፈልጉ ብቁ የሰው ኃይሎችን በማፍራት ያለውን አስተዋጽኦ በተግባር እያረጋገጠ መሆኑንም ገልጸዋል።
የSTEM የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርቱ ከሐምሌ 20/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለ45 ቀናት የሚቆይ ሲሆን፣ በተግባራዊ ሙከራዎች፣ በላቦራቶሪ ሥልጠናዎች እና በተለያዩ የፈጠራ ክንውኖች ተማሪዎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ እንደሚያስችል ተገልጿል።
ስለዩኒቨርሲቲዉ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የማህበራዊ ትስስር ገፆቻችንን ይከተሉ!
Website: www.asu.edu.et
Facebook: https://www.facebook.com/AssosaUniversityOfficial
Telegram: https://t.me/+J9ZDxvCigO0yN2Nk
Email: pir@asu.edu.et