





የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው በዩኒቨርሲቲው እየተከናወኑ ያሉ የተለያዩ የልማትና የማሻሻያ ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም ዩኒቨርሲቲው እያከናወነ ያለውን የተማሪዎች መኖሪያ ቤቶች የማዘመንና የእድሳት (Renovation) ሥራ፣ የአዳሪ ትምህርት ቤት መማሪያ ክፍሎች፣ የተማሪዎች መመገቢያ አዳራሾች እና የመኝታ ክፍሎችን በመዘዋወር ተመልክተዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል ከነበረበት የንፅህናና የአካባቢ ገጽታ ችግር አሁን ላይ ለውጥ መታየቱን ገልፀዉ ይህ ለዉጥ እንዲመጣ ያደረጉትን የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ያሬድ ሙሉንና ከእርሳቸው ጋር በቅርበት እየሠሩ ያሉ የዩኒቨርሲቲውን አመራሮችና ሠራተኞች አመስግነዋል። የተጀመረው ሥራ መልካም ጅምር የሚያሳይ በመሆኑ በቀጣይም በበለጠ ተጠናክሮና ተቋማዊ መልክ ተይዞ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች የዕውቀት፣ የምርምርና የፈጠራ ማዕከላት መሆናቸውን ያነሱት ትምህርት ሚኒስትሩ፣ አሶሳ ዩኒቨርሲቲም በአካዳሚያዊ ሥራዎችና በምርምር ላይ በማተኮር ጥራት ያለው ሰው ኃይል ከማፍራት ባሻገር ለአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ለክልሉና ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚጠቅም ሥራ ማከናወን እንደሚገባው ገልጸዋል።
ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በተለያዩ የተፈጥሮ ሀብቶች የበለፀገ ክልል መሆኑን በመግለጽም፣ የዩኒቨርሲቲው ምሁራንና ተመራማሪዎች በምርምር ሥራዎቻቸው የአካባቢውን ፀጋዎችና ችግሮች በማጥናት ለማኅበረሰቡ፣ ለክልሉና ለሀገር ተጨባጭ ጥቅም የሚያመጡ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል። ከክልሉ መንግሥትና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋርም በዕውቀትና በምርምር ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ትስስር መፍጠር እንዳለበት ገልጸዋል።
የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ያሬድ ሙሉ በበኩላቸዉ ትምህርት ሚኒስትሩ ላደረጉት ጉብኝት አመስግነው፣ ወደ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንትነት ከተመደቡ ጀምሮ በአጭር ቀናት በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑ ሥራዎችን ሪፖርት ለዩኒቨርሲቲዉ ሰኔት አባላት እና ለትምህርት ሚኒስትሩ አቅርበዋል።
በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሠራተኞች የበረሃ አበል ጉዳይ፣ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል መሬት አቅርቦት እና የጤና ኮሌጁ የትኩረት መስክ (Focus Area) እንዲታይላቸው ጠይቀዋል። በመጨረሻም የትምህርት ሚኒስትሩ በዩኒቨርሲቲው ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡
ጥበብን በተግባር!
ስለ ዩኒቨርሲቲዉ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን
Twitter:Assosa University (@AssosaU) / X
WhatsApp group: https://whatsapp.com/channel/0029Vau844l9xVJkZ3GXR21P
Facebook: https://www.facebook.com/AssosaUniversityOfficial
Telegram: https://t.me/+J9ZDxvCigO0yN2Nk
Email: pir@asu.edu.et