አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት የአካባቢ፣ ደን ሀብት ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር “አካባቢ ጥበቃ ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ-ቃል ክልላዊ ሲምፖዚየም አካሂዷል፡፡
የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ከማል አብዱራሂም ለሲፖዚየሙ ተሳታፊዎች ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አሶሳ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢ እና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ መስክ የማህበረሰቡን ምርት እና ምርታማነት የሚያሳድጉ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን አካባቢን ከመጠበቅ አኳያም ማዕድን አምራቾች ጎጂ የሆኑ ኬሚካሎችን ከመጠቀም ይልቅ አማራጭ ቴክኖሎጅዎችን መጠቀም እንዲችሉ ተደጋጋሚ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች መሠጠታቸዉን ተናግረዋል።
ዶ/ር ከማል አክለዉም የአካባቢ ብክለትን በመቀነስ ፅዱ እና ለነዋሪዎች ምቹ አካባቢን ለመፍጠር ለአካባቢ ብክለት መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዮችን ምሁራን በምርምር በመለዬት ሚናቸዉን መወጣት እንደሚገባቸዉ አሳስበዋል፡፡
የክልሉ ዋና አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ አስካል አልበሮ በበኩላቸዉ በክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እየተስፋፋ እንደሚገኝ ገልፀዉ በተለይ ከወርቅ ቁፋሮ ጋር ተያይዞ አገልግሎት ላይ እየዋለ የሚገኘዉ አካባቢ በካይ ኬሚካሎች በማህበረሰቡ ዘንድ ሊያስከትሉት የሚችለዉን አሉታዊ ተፅዕኖ በተጠኑ ጥናቶች በመወያየት መፍትሔ ማበጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት የአካባቢ፣ ደን ሃብት ጥበቃና የአየር ንብረት ለዉጥ ባለስልጣን ኃላፊ ክቡር አቶ ሉቁማን አብዱልቃድር እንደገለፁት ክልሉ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ማምረቻ ቦታዎች እና በማዕድን ማምረቻ አካባቢዎች የአካባቢ ተፅዕኖ ቅነሳ ስራዎች በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በሲፖዚየሙ በዩኒቨርሲቲዉ መምህራን በመ/ር መሀመድ ኢብራሂም Investigation of Toxic Heavy Metal Pollution in a Gold Mining Site at Kurmuk and Sherkole woredas of Assosa zone,B/G/R/S እና በዶ/ር ታደለ ዳንኤል Restoring Degraded Landscapes in Abandoned Mining Areas of Kurmuk District, B/G/R/S, Ethiopia በሚሉ ርዕሶች ጥናታዊ ፁህፎች ቀርበዉ ሰፊ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በሲፖዚየሙ የተለያዩ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲዉ አመራሮች፣ በክልሉ በአካባቢ ጥበቃና ተፈጥሮ ሀብት የሚሰሩ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የማዕድን አምራቾች ተሳትፈል፡፡
በመጨረሻም የምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብዱልሙህሲን ሀሰን እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች የማጠቃለያ ዉይይቱን የመሩ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ ሀሳቦች ማብራሪያ እና ምላሽ ሰጥተዉ ተጠናቋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን
Twitter:Assosa University (@AssosaU) / X
WhatsApp group: https://whatsapp.com/channel/0029Vau844l9xVJkZ3GXR21P
Telegram: https://t.me/+J9ZDxvCigO0yN2Nk
Email: pir@asu.edu.et






