በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ 22ኛዉ ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን “ትዉልድን በሥነ-ምግባር፤ ተቋምን በአሠራር!” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ኩኔቶች ተከብሯል።
በዩኒቨርሲቲዉ ለ7ኛ ጊዜ ዛሬ ህዳር 25/ 2018 ዓ.ም የተከበረዉ 22ኛዉ ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን ከክልሉ ተጋባዥ እንግዶች፣ ባለድርሻ አካላት እና የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ የተከበረ ሲሆን በክብረ በዓሉ ላይ የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ከማል አብዱራሂም ተገኝተዉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የእዉቀት፣ የክህሎት እና የመልካም ሥነ-ምግባር መሸመቻ ሥፍራ መሆኑን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ አሁን ላይ እዚህም እዚያም የሚስተዋሉ ችግሮች ምንጫቸዉ ከሥነ ምግባር ጉድለት ጋር የተያያዙ መሆኑን ጠቁመዋል። ክፍተቱም እንዲታረም በትዉልድ ሥነ ምግባር ላይ በደንብ መሥራት ያስፈልጋል ብሏል። የሙስና መንስኤ ብልሹ ሥነ ምግባር እንደሆነ ያወሱት ዶ/ር ከማል ችግሩን ከሥር መሠረት ለመፍታት ከግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ባሻገር ጠንካራ የአሰራር ሥርዓት ማበጀት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
ለሙስናና ብልሹ አሠራር የሚስተዋልባቸዉ የሥራ ክፍሎችን በጥናት ላይ የተመሠረተ የእርምት እርምጃ መዉሰዱን የገለፁት ዶ/ር ከማል እንደ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ የሚናከናዉናቸዉ ሥራዎች ዲጂታላይዝ በማድረግ ለሙስናና ብልሹ አሠራር ተጋላጭነት ማስቀረት መቻሉን ጭምር ተናግረዋል።
የቤ/ጉ/ክ ፍትህ ቢሮ ምክትል ሓላፊ አቶ አስማማዉ አብሸኮ በሰጡት ሀሳብ “የሙስና ትግል ከእራስ ይጀምራል! ዩኒቨርሲቲዉ ችግሩን ለማስቀረት እያከናወነ ያለዉ ቁርጠኝነቱን ያሳያል” ብሏል።
የክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ነጅመድን አልማሃዲ በበኩላቸዉ በሀገራችን ሙስና ህዝብን እና መንግሥትን እያጋጨ መሆኑን ጠቁመዉ አሠራሮቻችን ዲጂታላይዝ ማድረግ ላይ ትኩረት ማድረጉ ሥራ ወሳኝ እንደሆነ ገልፀዋል።
ክብረ በዓሉ በሠራተኞች መካከል በተካሄደው ጥያቄና መልስ ዉድድር፣ በሙስና ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እና ዉይይት ታጅቦ የተከበረ ሲሆን በማጠቃለያዉ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ያስመዘገቡትን ሀብት በታዳሚዉ ፊት ለሥነ ምግባር መከታተያ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ያየህራድ አጥናፉ አስረክበዋል።
በመጨረሻም በተካሄደው የጥያቄና መልስ ዉድድር ለተሳተፉ ሠራተኛች የእዉቅናና ሽልማት ሥነ ሥርዓት ተካሂዶ አቋም መግለጫ በመያዝ ፕሮግራሙ ተጠናቋል።
ተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማህበራዊ ትስስር ገፆቻችን ይከተሉን
Twitter:Assosa University (@AssosaU) / X
Website: www.asu.edu.et
WhatsApp group: https://whatsapp.com/channel/0029Vau844l9xVJkZ3GXR21P
Telegram: https://t.me/+J9ZDxvCigO0yN2Nk
Email: pir@asu.edu.et






