(መጋቢት23/2015 ዓ/ም ) የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራው በተጨማሪ በቤ.ጉ.ክልል ውስጥ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች፣አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶችና ህፃናት እና ሌሎች ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ሶስት ማዕከላትን በመክፈት ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ሥራዎችን በመስጠት ላይ መሆኑ ይታወቃል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ቤት ከ”UNHCR” ጋር በመተባበር ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት አድማሱን በማስፋት በአሶሳ ዞን እና መተከል ዞኖች ቢሮዎችን በመክፈት ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችና ተመላሾች አገልግሎቱን በመስጠት የፍትህ መብታቸው እንዲረጋገጥላቸው የሚያስችለውን አድስ ፕሮጀክት ዛሬ በአሶሳ እና በግልገል በለሰ ከተሞች አስጀምሯል ።
የፕሮግራሙ ዓላማም ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቱን በመስጠት የፍትህ ተደራሽነቱን በማስፋት የሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበርና የሕግ የበላይነቱ እንዲረጋገጥ ለማስቻል የተዘጋጀ የፕሮጀክት ማስጀመሪያ መድረክ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በፕሮግራሙ ላይም ከ”UNHCR” ቢሮ ተወካይ፣የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ፍትሕ ቢሮ ኃላፊዎች እንድሁም ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተውበታል።