Assosa University

ዩኒቨርሲቲው የሚሰጠዉን ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት በተመለከተ አመታዊ ወርክሾፕ አካሄደ

ወርክሾፑ የተዘጋጀዉ በዩኒቨርሲቲዉ የማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት በህግ ትምህርት ቤት ድጋፍ ለሚሹ እና ለተፈናቃይ ወገኖች የሚሰጠዉን ነጻ የህግ አገልግሎት አፈጻጸም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመገምገም በቀጣይ ለሚሰሩ ሥራዎች አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነዉ።
 
የምክክር መድረኩ በአሶሳ ዞን ስር የሚገኙ ወረዳዎች እና የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ዳኞች፣አቃቢያን ህግ ፣የጠበቆች ማህበር ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲዉ ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ የስራ ክፍሎች ሀላፊዎች፣ አገልግሎቱን የሚሰጡ የህግ ት/ቤት መምህራን እና የሀገር ዉስጥ ተፈናቃይ ተወከዮች በተገኙበት ተካሂዷል።
 
በምክክር መድረኩ ለተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲዉ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብደልሙህስን ሀሰን ዩኒቨርሲቲዉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የማህበረሰቡን ችግሮች የሚፈቱ ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ገልጸዉ በነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎቱ ፍትህ አቅም ላላቸዉ ነዉ ተብሎ የሚገመተዉን የተሳሳተ ግምት እንድቀር በማድረግ አቅም ለሌላቸዉ ወገኖችም በነጻ የህግ አገልግሎት ድጋፍ ተጠቃሚ እንድሆኑ ያደረግንበት ተግባር ነዉ ብለዋል።
 
በመድረኩ ላይ የዩኒቨርሲቲዉ ነጻ ድጋፍ የህግ አገልግሎት አፈጻጸም አጭር ሪፖርት በመምህር ኪዳኔ ደያሳ በኩል እና የክልሉ ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ማህበር የሥራ እንቅስቃሴ በመምህር ሰለሞን ኢታንሳ ቀርበዋል።
 
ሪፖርቶቹ ከቀረቡ በኋላ በዶ/ር አብደልሙህስን ሀሰን፣በክልሉ ፍትህ ቢሮ ሀላፊ በአቶ መሃመድ ሀሚድ እና በአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በአቶ መሃመድ ሙሃመድ መድረኩ እየተመራ ዉይይት ተካሂዷል።
 
በዉይይቱ ላይም ዩኒቨርሲቲዉ ህግ እንድከበር፣ንቃተ ህግ እንድስፋፋ እና አቅም ለሌላቸው ወገኖች መመኪያ መሆን መጀመሩ የሚያበረታቱ ሥራዎች መሆናቸው ተነስቷል።
በመጨረሻም ዩኒቨርሲቲዉ ይህንን ሥራ ሲሠራ ከጎኑ ለነበሩት ለተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ከፍተኛ ኮሚሽን(UNHCR)፣ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት እና ለክልሉ ፍትህ ቢሮ የእዉቅና ምስክር ወረቀት በመስጠት መርሃ ግብሩ ተጠናቋል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን
Twitter:Assosa University (@AssosaU) / X
Email: pir@asu.edu.et

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *