የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ባደረገላቸው የግብዓት እና የሙያ ድጋፍ በመታገዝ የተሻለ የስንዴ ሰብል ማልማታቸውን በአሶሳ ዞን የባንባሲ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።
የባንባሲ ወረዳ አፋፍር በናሬ ቀበሌ ነዋሪዎቹ ለስንዴ ልማት አዲስ ቢሆኑም በ31 ሔክታር ማሳ ላይ በኩታ ገጠም ያለሙት የበጋ ስንዴ በጥሩ ቁመና ላይ ይገኛል።
ለአርሶ አደሮቹ የዘር፣ የማዳበሪያ እና የሙያ ድጋፍ በማድረግ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል።
በወረዳው የስንዴ ልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው የጎበኙት የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ወ/ሮ ዓለምነሽ ይባስ እና የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢስሐቅ አብዱልቃድር፣ በክልሉ የስንዴ ልማት ሥራ በአርሶ አደሩ እና በአመራሩ ቁርጠኝነት የተሻለ ውጤት እየታየበት መሆኑን ገልጸው የአሶሳ ዩኒቨርሲቲም ለአርሶ ላበረከተው የሙያ እና የግብዓት ድጋፍ አመስግነዋል።
ዩኒቨርሲቲው የጀመራቸውን ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች አጠናክሮ እንዲቀጥል አመራሮቹ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ከማል አብዱረሂም፣ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን አርሶ አደሩን በተለያዩ ዘርፎች እያገዘ መሆኑን ገልጸው፣ በተለይ በስንዴ ልማት የተጀመረውን ሙያዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።