ዩኒቨርሲቲዉ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 2,182 ተማሪዎች አስመረቀ (ጥር 09/2013 ዓ.ም፣ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ፣ አሶሳ) ****** ****** የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በ2012 ዓ.ም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክኒያት ሳይመረቁ የቀሩት ተማሪዎቹን አስመረቀ፡፡ ዩኒቨርሲቲዉ በ7 ኮሌጆች እና በሶስት ትምህርት ቤቶች በ38 የትምህርት ፕሮግራሞች በመደበኛ መርሃ ግብር፣ በርቀትና ተከታታይ ትምህርት እንዲሁም በድህረ ምረቃ ፕሮግራም ያስተማራቸውን 2,182 ተማሪዎች በዛሬዉ ጥር 09/2013 ዓ/ም በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል፡፡ በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታና የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አወል ወግሪስመሀመድ፣ የአሶሳ ከተማ ከንቲባና የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢ አቶ ዑመር መሀመድ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡ በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ከማል አብዱረሂም ለተመራቂ ተማሪዎች እና እንግዶች ባስተላለፉት መልዕክት የCOVID-19 ወረርሽኝ ፕሮቶኮል መርህ መሰረት ትምህርታቸዉን ማጠናቀቅ በመቻላቸዉ የተሰማቸዉን ልባዊ ደስታ ገልፀዉ ምሩቃኑ ራሳቸዉንና ጓድኞቻቸዉን ከዚህ አስከፊ በሽታ በመጠበቅ በዕውቀት፣ በክህሎት እና በአመለካከት ታንጸዉ ለመጡለት ዓላማ በመብቃታቸዉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በዕለቱ ዩኒቨርሲቲው በከፊተኛ ዉጤት ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 18 የሚሆኑ ሰቃይ ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው በረዳት ምሩቃን ተቀጥሮ እንዲያገለግሉ መወሰኑን ዶ/ር ከማል አብዱራሂም ገልፀዋል፡፡