Assosa University

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አራተኛው ክልላዊ የምሁራን ጉባኤ ተካሄደ

“ሰላም እና አካታች ልማትን ለማረጋገጥ የምሁራን ሚና” በሚል ርዕስ ለአራተኛ ጊዜ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ክልላዊ የምሁራን ጉባኤ ተካሂዷል።

በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ከማል አብዱራሂም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዕዉቀት ማፍለቂያ ማዕከላት፣ የፖሊሲ ድጋፍ አቅራቢዎች እና ለማህበረሰብ ለውጥ አንጋቢ የሆኑ ሀሳቦች የሚወጡበት መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲዉም በሰላም፣ በልማት እና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እያካሄደ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ ምሁራን እዉቀታቸዉን፣ ልምዳቸዉን እና ሙያዊ ሓላፊነታቸዉን ተጠቅመዉ ለሀገር ሰላምና ልማት የበኩላቸዉን ድርሻ መወጣት እንደሚገባቸዉ ዶ/ር ከማል አሳስበዋል፡፡

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ክቡር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸዉ ሰላም ህይወት ላለዉ ነገር ሁሉ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዉ በክልሉ እየታየ ያለዉ ሰላም የክልሉ ማህበረሰብ እና የምሁራን ጥረት እንደሆነም ተናግረዋል። ሠላምን ለማረጋገጥ የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ምሁራን ጥናትና ምርምር በማድረግ እና ከክልሉ ጋር ተቀናጅቶ በመስራት የሀገርን ልማት ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸዉ አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲዉ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዑመር ሸሪፍ በመክፈቻ ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር መስኮች ላለፉት 14 ዓመታት በርካታ ስራዎችን እንደሰራ ተናግረዋል።

በዘንድሮው ዓመትም 26 ጥናትና ምርምሮች እና 12 የማህበረሰብ ጉድኝት ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው ዓለም አቀፍ የምርምር ግንኙነቱንና አጋርነቱን በማስፋት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር በመስራት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

ምሁራን በምርምር የተደገፉ መፍትሔ ሀሳቦችን ለህብረተሰብ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በአካባቢያዊ እና በፖለቲካዊ መስኮች በማቅረብ ኃላፊነት እንዲወጡ ዶ/ር ዑመር ሸሪፍ አሳስበዋል።

በጉባኤው በዶ/ር አበበ አኖ እና በመ/ር መሀመድ ኢብራሂም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም፣ አካታችነት እና የምሁራን ሚና እና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ዘላቂ ሠላምና ሁለንተናዊ ልማት ለማረጋገጥ ምሁራን የተቀናጀ ተሳትፎና ስትራቴጂካዊ ሚና የሚሉ ሁለት ጥናታዊ ፁህፎች ቀርበዋል፡፡

በቀረቡ ሰነዶች ዙሪያ አስተያቶችና ጥያቄች ከተሳታፊዎች የቀረቡ ሲሆን በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ክቡር አቶ ጌታሁን አብዲሳ፣ ዋና አፈ-ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ አስካለች አልቦሮ እና በዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ከማል አብዱራሂም አወያይነት ጥልቅ ዉይይት ተካሂዶበታል፡፡

በዉይይቱ ማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ ክብርት ወ/ሮ አስካለች አልቦሮ ባስተላለፉት መልዕክት ሁሉም ምሁራን በተሰማሩበት የሥራ መስክ ለሠላም ቅድምያ መሥጠት እንዳለባቸዉ አስምሮበታል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ የማህበራዊ ገፆቻችን ይከተሉ

Twitter:Assosa University (@AssosaU) / X

Website: www.asu.edu.et

WhatsApp group: https://whatsapp.com/channel/0029Vau844l9xVJkZ3GXR21P

Facebook: https://www.facebook.com/AssosaUniversityOfficial

Telegram: https://t.me/+J9ZDxvCigO0yN2Nk

Email: pir@asu.edu.et

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *